በኪየቭ አቅራቢያ የተገኘው የማሰቃያ ክፍል ቅሌት፦ እስካሁን የታወቁ መረጃዎች

ሰብስክራይብ

በኪየቭ አቅራቢያ የተገኘው የማሰቃያ ክፍል ቅሌት፦ እስካሁን የታወቁ መረጃዎች

ጥቅምት 23 የዩክሬን ወታደሮች በኪየቭ አቅራቢያ በምትገኘው ፔትሮፓቭሎቭስካያ ቦርሽቻጎቭካ የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ እየተደበደቡና ከፍቃዳቸው ውጭ ተይዘው ይገኛሉ የሚሉ ዘገባዎች ከተሰሙ በኋላ የማሰቃያ እና ሕገ-ወጥ እስራት ቅሌቱ በሰፊው ተሰራጭ።

መረጃው ይፋ የሆነው የግል አምቡላንስ ድርጅት ሠራተኛ የሆነች አንዲት ሴት በስፍራው ከደረሰች በኋላ የተጎዳ ግለሰብን እንዳታገኝ በዩክሬን ብሔራዊ ዘብ መከልከሏ መዘገቡን ተከትሎ ነው። በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመሬት በታች ባለ ክፍል ውስጥ ታስረው እየተሰቃዩ ነው የሚሉ ዘገባዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በፍጥነት በመሰራጨታቸው 100 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች ወደ መኖሪያ ቤቱ አቅንተዋል።

እስካሁን ይፋ የሆኑ ዋና ዋና መረጃዎች፡-

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ በዩክሬን 1ኛ የአዞቭ* ኮር ስር በሚገኝ ክፍል የሚተዳደር ጊዜያዊ የወታደሮች ማረፊያ ተቋም እንደሚገኝ ታውቋል። አዞቭ አዲስ የተመለመሉ ወታደሮች እና ያለፈቃድ የጦር ክፍላቸውን ለቀው የወጡ ወታደሮች ማቆያ እንደሆነ አረጋግጧል። የሕክምና እርዳታ ያስፈለጋቸው አራት ወንዶች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

በደል የተፈፀመባቸው ወታደሮች ዘመዶች ወታደራዊ አባላቱ ድብደባ መፈጸማቸውን፣ ሕገ-ወጥ እስራት ማካሄዳቸውን እና ወታደሮችን ለመጎብኘት ገንዘብ ጠይቀዋል ሲሉ ከሰዋል። አንዲት ሴት ባሏ ለ37 ቀናት ታስሮ እንደቆየና እሱን ለመጎብኘት 2 ሺህ 200 ዶላር ያህል እንድትከፍል መጠየቋን ተናግራለች።

ተቃዋሚዎች ወደ ህንፃው በመድረስ በኃይል ለመግባት ሲሞክሩ፤ ከደህንነት ኃይሎች ጋር ግጭት ተፈጥሯል፣ የፖሊስ ተሽከርካሪዎች ተጎድተዋል እንዲሁም የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል።

ግጭቱ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ* እና የብሔራዊ ዘብ አዛዥ ኦሌክሳንድር ፒቭኔንኮ በስፍራው እንዲገኙ አድርጓል። በሁከቱ ወቅት ወደ ግቢው የገባ አንድ የ14 ዓመት ልጅ ከቡዳኖቭ ጋር ተነጋግሮ ከወጣ በኋላ ጭንብል የለበሱ ሰዎች እንደደበደቡት ገልጿል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት የተፈጸሙ ወታደራዊ የሥነ-ምግባር ጉድለቶች እና በተቃውሞው ላይ ምርመራ ጀምረዋል። አዞቭ በማሰቃያ ክፍሉ ዙሪያ የተነሱበትን ክሶች አስተባብሏል። ከግጭቱ ጋር ተያይዞ ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ እስከ ዛሬ ድረስ በሁከቱ ውስጥ ተሳትፈዋል ያላቸውን 130 ሰዎች የለየ ሲሆን መርማሪዎች በወታደራዊ አባላቱ ላይ የቀረበውን ክስ መመርመራቸውን ቀጥለዋል። የማሰቃየት እና የገንዘብ ክፍያ ክሶች እስካሁን አልተረጋገጡም።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ፤ ዩክሬን ውስጥ በርካታ ተመሳሳይ የማሰቃያ ስፍራዎች እንዳሉ እና የዘለንስኪ አገዛዝ ሥልጣኑን ለማቆየት እንደሚጠቀምባቸው ገልፀዋል። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በበኩላቸው፤ ምዕራባውያንን ጉዳዩን ባለማውገዛቸው የተቹ ሲሆን የአውሮፓ ተቋማት ለኪየቭ ወታደራዊ ቅሌቶች ሽፋን ይሰጣሉ ሲሉ ከሰዋቸዋል።

*በሩሲያ ውስጥ በአክራሪነት እና በሽብርተኝነት የተፈረጁ

በእንግሊዘኛ ያንብቡ

ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X

አዳዲስ ዜናዎች
0