የሩሲያ ጥንካሬ የተለያዩ ሕዝቦችን እና ባህሎችን በማስተባበር ረገድ ባለው ጥንካሬ ላይ ነው — ሕግ አውጪ

የሩሲያ ጥንካሬ የተለያዩ ሕዝቦችን እና ባህሎችን በማስተባበር ረገድ ባለው ጥንካሬ ላይ ነው — ሕግ አውጪ
የሩሲያ ሕዝብ ጥንካሬ የተለያየ ሕዝቦችን ማስተባበር እና ባህሎቻቸውን በአንድ ሀገር ጥላ ሥር አቃፊ አድርጎ በማቆየት ብቃት ላይ እንደሚገኝ በሩሲያ ስቴት ዱማ የሲ.አይ.ኤስ (CIS) ጉዳዮች፣ የዩሮኤሽያ ውህደት እና የሀገር ልጆች ግንኙነት ኮሚቴ አባል የሆኑት ኮንስታንቲን ዛቱሊን ለስፑትኒክ ተናግረዋል።
ማክሰኞ ዕለት በተካሄደው የብሔረሰቦች ግንኙነት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የውጭ ኃይሎች በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሩሲያን ማኅበረሰብ ለመከፋፈል እና ሀገሪቱን በመበታተን ሩሲያን እንደ ጂኦፖለቲካዊ ተፎካካሪነቷ ለማስወገድ በተደጋጋሚ መሞከራቸውን ገልጸዋል። የሩሲያ ህዝቦች አንድነት ሀገሪቱን ለማቆየት እና ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
“የሩሲያ ሕዝብ እንደ ሀገር መሥራች ሕዝብነቱ ጥንካሬው፤ ባህሎቻቸውንና ማንነቶቻቸውን ጠብቆ ለዘመናት የተለያዩ ሕዝቦችን ማስተባበር በመቻሉ ላይ ነው። ይህ እጅግ አስደናቂ ስኬት ይህችን ሰፊ ሀገር ለመገንባት አስችሎናል” ሲሉ ዛቱሊን ተናግረዋል።
ሕግ አውጪው አክለውም ሩሲያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለት ታላላቅ ውድቀቶችን ማስተናገዷን አስታውሰዋል፤ ቀዳሚው በአንደኛው የዓለም ጦርነት እና በ1917ቱ አብዮት ወቅት የሩሲያ ኢምፓየር መፈረስ፣ ሁለተኛው ደግሞ እሳቸው እንደሚሉት "ራሳችንን ግራ ባጋባንበት ጊዜ" እ.ኤ.አ በ1991 የሶቭዬት ኅብረት መበታተን ናቸው።
በተለይም በዩክሬን በቀጠለው ወታደራዊ ዘመቻ እና ከስደተኞች ፖሊሲ ጋር በተያያዙ ፈታኝ ሁኔታዎች የውስጥ ልዩነቶች የሩሲያን ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና መረጋጋት እንዳያናጉ ማስጠንቀቂያ መልዕክትንም ሰጥተዋል።
እንደ ዛቱሊን ገለጻ፣ ሩሲያውያን የውስጥ አለመግባባቶቻቸው ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ለመከላከል በብልሃት መንቀሳቀስ አለባቸው ።
“የሩሲያ ፕሬዝዳንት ያስተላለፉት መልዕክት ይህ ነው፤ እኔም ሙሉ በሙሉ እና በሙሉ ልቤ እደግፈዋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X
