ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ላይ ጫናዎችን እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበች
11:29 13.11.2025 (የተሻሻለ: 11:34 13.11.2025)

© telegram sputnik_ethiopia
/ ሰብስክራይብ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኤርትራ ላይ ጫናዎችን እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበች
ጥሪው የቀረበው ትኩረቱን በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ባሉ ወቅታዊ ተለዋዋጭ የፖለቲካና የደህንነት ሁነቶች ላይ አድርጎ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመካሄድ ላይ ባለው የውይይት መድረክ ነው።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ተሻሽሎ የነበረው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት በአስመራው መንግሥት ጸብ አጫሪ ድርጊቶችና ትንኮሳዎች ምክንያት እየሻከረ መምጣቱን ስብሰባውን የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ገልጸዋል ሲል የስፑትኒክ አፍሪካ ባልደረባ ዘግቧል።
በተለይ ኢትዮጵያ የወደብና የባሕር በር ጥያቄዎችን ማንሳቷን ተከትሎ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ መሻከሩን በማንሳት፤ የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስና እድገቷን ለማደናቀፍ ታጣቂዎችን ከመደገፍና ከማስታጠቅ ጀምሮ ዐይነተ ብዙ ትንኮሳዎች እያደረገ እና የውጭ አካላት ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።
"በሉዓላዊነታችንና በብሔራዊ ጥቅማችን እየተቃጣ ለሚገኘው ጣልቃ ገብነት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ምክንያት ቢኖረንም ሁኔታውን በትዕግስት መከታተልን መርጠናል" ሲሉም ተናግረዋል።
በሀገራቱ መካከል የተፈጠረው የተካረረ ቅራኔ ምጣኔ ሀብትን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች ሊደረጉ በሚችሉ የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትብብሮች ሊፈታ እንደሚችልም ገልጸው፤ ሁለቱም ሀገራት ይህን ለማሳካት የሚያስችል ደማዊና ታሪካዊ ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው አብራርተዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X


