ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የምርጫ ሂደትን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋገጠች
10:00 28.11.2026 (የተሻሻለ: 10:04 28.11.2026)

© telegram sputnik_ethiopia
ሰብስክራይብ
ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የምርጫ ሂደትን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋገጠች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሴሲሊያ አዱት ማንዮክ አዴንግን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይቱም ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነትና የሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር እንዲሁም የከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝቶችን ማሳደግ ላይ ተወያይተዋል።
ዶ/ር ጌዲዮን ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን የሚካሄደውን መጪ ምርጫ ሂደት በቅርበት እየተከታተለች መሆኑን ገልጸው፣ ሂደቱን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
አምባሳደር አዴንግ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላምና ደኅንነት ለማስፈን ላበረከተችው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፣ የኢትዮጵያ ድጋፍ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀው፣ በተለያዩ የሙያ መስኮችና ተቋማት እያበረከቱ ላለው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X