የስፑትኒክ ማዕከላት በታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ መከፈት አፍሪካውያን እውነተኛ መረጃ የሚያገኙበትን ዕድል ለማስፋት ይረዳል - ላቭሮቭ

ሰብስክራይብ
ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል እና የሬዲዮ ጣቢያ የሆነው ስፑትኒክ ዛሬ ጥቅምት 10 ቀን 2019 ዓ.ም፣ በዳሬሰላም እና በጆሃንስበርግ ሁለት ሁለገብ የዝግጅት ክፍሎችን ከፍቷል።

በታንዛኒያ ዋና ከተማ የተካሄደው የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የቪዲዮ መልዕክት ጀምሯል።

"በዳሬሰላም እና በጆሃንስበርግ የቀጣናው ቢሮዎች መከፈታቸው፣ አፍሪካውያን ታዳሚዎች ማንኛውም ያልተዛባ፣ ከርዕዮተ ዓለም ተጽዕኖ ነፃ የሆነ፣ ትክክለኛና የተረጋገጠ መረጃን በስፋት እንዲያገኙ ይረዳል" ሲሉ ገልጸዋል።

አክለውም፣ ለታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ድጋፍ ለጋዜጠኞች ውጤታማና ደህንነቱ የተጠበቀ ሥራ እጅግ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዛሬ 'የተባበሩት ምዕራባዊያን' እንደ ሳንሱር እና 'አድሎአዊ አሰራሮችን' የመሳሰሉ ዘዴዎችን በመጠቀም በዓለም አቀፍ የመረጃ ዐውድ ላይ ልዩ ልዩ ድምጾችን በጽኑ በሚያፍኑበት በአሁኑ ወቅት፣ የመሰል ሥራ ዋጋ እጅግ የጎላ ነው" ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።

ሰርጌ ላቭሮቭ የሁለቱ አዳዲስ የስፑትኒክ ቢሮዎች መከፈት፣ በጥቅምት 18-19 2019 ዓ.ም. በሞስኮ ከሚካሄደው እና በሩሲያና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የበለጠ ያጠናክራል ተብሎ ከሚጠበቀው ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ዋዜማ ጋር መገጣጠሙ ልዩ ትርጉም እንዳለው ጠቁመዋል።

በአፍሪካ እያደገ የመጣው የስፑትኒክ ኑባሬ አስፈላጊነት በደቡብ አፍሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ፖል ማሻቲሌም ጎልቶ ተነስቷል።

በጆሃንስበርግ የስፑትኒክ ቀጣናዊ ቢሮ መከፈት ለደቡብ አፍሪካ እና ለጠቅላላው የአፍሪካ አኅጉር የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪ ትልቅ እድገት ነው። ይህም በደቡብ አፍሪካ እና በሩሲያ መካከል እያደገ የመጣውን ትብብር የሚያንፀባርቅ ከመሆኑም በላይ፣ ለነቃና ዲሞክራሲያዊ ለሆነ የሕዝብ ውይይት አስፈላጊ ለሆኑት የድምጾችና የዕይታዎች ብዝኃነት አስተዋፅኦ ያደርጋል። ስፑትኒክ የአፍሪካውያንን ድምፅ ለማጉላትና የአፍሪካን ታሪኮች ለመናገር የገባውን ቃል እንቀበላለን። የጆሃንስበርግ ቢሮዎቻችሁ ለገንቢ ውይይት፣ ጥራት ላለው ጋዜጠኝነት እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ፣ በሩሲያ እና በአፍሪካ አኅጉር መካከል ላለው ጠንካራ ግንኙነት መድረክ ሆኖ እንዲያገለግል እመኛለሁ።

የስፑትኒክ እናት ኩባንያ ሮሲያ ሴጎድኒ' የሜዲያ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተር ዲሚትሪ ኪሴሌቭ በበኩላቸው፣ "በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በቀጥታ የመሥራት ዕድል ማግኘት የጽኑ እምነት ማረጋገጫ ነው፤ በሀገራት፣ በሕዝቦች፣ እንዲሁም በጋዜጠኞችና በታዳሚዎቻቸው መካከል ያለ እምነት ምስክር ነው። ይህ እምነት ደግሞ የአፍሪካንም ሆነ የሩሲያን የመረጃ ልዓላዊነት ያጠናክራል" ብለዋል።

የስፑትኒክ የመረጃ ማዕከላት በደርዘን የሚቆጠሩ የአካባቢው ጋዜጠኞችን ያቀፉ ሙሉ የዝግጅት ክፍሎች ናቸው።

በጆሃንስበርግ እና በዳሬሰላም የሚገኙት አዳዲስ የዝግጅት ክፍሎች፣ ይዘቶች በእንግሊዝኛ እና በስዋሂሊ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። ይህም በመላው አኅጉሪቱ በሚገኙ የሬዲዮ ጣቢያዎች የሚተላለፉ ፖድካስቶችን የሚያካትት ሲሆን፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አዳማጮች ይደርሳሉ።


ስፑትኒክ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2022 የተጀመረ ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአፍሪካ ውስጥ ፓን- አፍሪካዊነት ላይ ትኩረት ከሚሰጡ ታዋቂ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አንዱ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት ስዋሂሊ፣ አማርኛ እና ኦሮምኛን ጨምሮ በአምስት ቋንቋዎች አገልግሎት ይሰጣል።

👉 ስፑትኒክ ከ30 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የሚያስተላልፍ እና በዓለም ዙሪያ 26 ሁለገብ የዝግጅት ማዕከላትን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል እና የሬዲዮ ጣቢያ ነው።
አዳዲስ ዜናዎች
0