ከአፍሪካ የሚገኙ የሕክምና እና የሥነ-ውበት መገለገያ የናኖ-ቅንጣቶች በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ጥናት ሊደረግባቸው ነው

ከአፍሪካ የሚገኙ የሕክምና እና የሥነ-ውበት መገለገያ የናኖ-ቅንጣቶች በሩሲያ እና በኢትዮጵያ ጥናት ሊደረግባቸው ነው
የሩሲያው ሴቫስቶፖል ስቴት ዩኒቨርሲቲ እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የትብብር ስምምነታቸውን በማሳደግ ሳይንቲስቶች በጋራ የሚያከናውኑትን አዲስ የምርምር ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።
ተመራማሪዎቹ ልዩ የቡና ዝርያዎችንና ሌሎች በአፍሪካ ብቻ የሚገኙ ዕፅዋትን በመጠቀም የሚመረቱ የናኖ-ቅንጣቶችን (ናኖ-ፓርቲክልስ) ለሕክምና፣ ለውበት መጠበቂያ እና ለተለያዩ ዘርፎች ለማዋል ጥናት እንደሚያደርጉ የሩሲያ ሚዲያ ዘግቧል።
የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ፊዚክስ ፕሮፌሰር እና የኢትዮጵያ ፊዚክስ ማኅበር ጸሐፊ ፕሮፌሰር አበበ በላይ በሩሲያው ዩኒቨርሲቲ የክብር ተጋባዥ ሳይንቲስት በመሆን ቀደም ሲል ምርምሩን ተቀላቅለዋል፡፡
ተመራማሪው ከዚህ ቀደም ከስፑትኒክ አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ናኖ-ተኮር ሥርዓቶችን በመጠቀም መድኃኒቶችን በማምረት ረገድ ጠቃሚ ልምድ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ጥናቱ በተለይም የካንሰር ሕክምና መድኃኒቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማድረስ እንዲሁም የብር ናኖ-ቅንጣቶችን በዕፅዋት አማካኝነት ለማምረት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል።
“ይህንን የመድኃኒት አቅርቦት ሥርዓት የምንሰራው ለሳይንሳዊ ጽሑፍ ሕትመት ወይም ለሌላ ነገር ብቻ ሳይሆን፣ የምርምሩን የመጀመሪያ ደረጃ ማሳያ (ፕሮቶታይፕ) ለማዘጋጀትም ጭምር አቅደናል። በመሆኑም ናኖቴክኖሎጂን በመጠቀም መድኃኒትን እንዴት ማድረስ እንደሚቻል በጣም ጥሩ ልምድ አገኛለሁ ብዬ እጠብቃለሁ።" ሲሉ ፕሮፍፌሰሩ አክለዋል፡፡
ይህ አጋርነት የሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች የቴክኖሎጂ አቅም የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ፣ ወጣት ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች በሩሲያ የማስተርስና የዶክትሬት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቁሟል።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት የበለጸገ ምስል
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X