የአሜሪካ የባሕር ኃይል በኢራን ላይ የሚጥለው እገዳ ከመጀመሩ በፊት የምናውቃቸው መረጃዎች
የአሜሪካ የባሕር ኃይል በኢራን ላይ የሚጥለው እገዳ ከመጀመሩ በፊት የምናውቃቸው መረጃዎች
አሜሪካ፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚገኙ የኢራን ወደቦች ላይ ከዛሬ 8:00 ሰዓት ጀምሮ የባህር ኃይል እገዳ እንደምትጀምር ዶናልድ ትራምፕ ይፋ አድርገዋል።
እንደ ማዕከላዊ ዕዝ መረጃ፣ አዲሱ እንቅስቃሴ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ ወይም የሚወጡ ማናቸውንም የባህር ላይ ትራፊክ ኢላማ የሚያደርግ ሲሆን፣ ከኢራን ጋር ግንኙነት የሌላቸው መርከቦች ግን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲቀጥሉ ይፈቀድላቸዋል።
የዋሽንግተን አቋም
▪ይህ እገዳ በቬንዙዌላ ላይ ከተጣለው እገዳ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ሲሉ ትራምፕ ገልፀዋል።
▪ የእገዳው ዓላማ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን መተው ጨምሮ አሜሪካ የምታቀርባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች እንድትቀበልና ወደ ድርድር እንድትመለስ ተጽዕኖ ለማድረግ መሆኑን ትራምፕ አስረድተዋል።
▪ትራምፕ ባወጡት የማሕበራዊ ሚዲያ ጽሑፋቸው፣ የኢራን መርከቦች አሜሪካ ወደ ጣለችው የሆርሙዝ ወሽመጥ እገዳ ከተጠጉ ይወገዳሉ ብለዋል፡፡
▪ኢራን የዋሽንግተንን ቅድመ ሁኔታዎች የማትቀበል ከሆነ የአሜሪካ ኃይሎች ጥቃታቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
▪በርካታ የኔቶ አባል ሀገራት በአሜሪካ የሚመራውን እገዳ ለመደገፍ ማቀዳቸውን ትራምፕ ተናግረዋል።
የቴህራን አቋም
▪የአሜሪካ ውሳኔ ሕገ-ወጥና የባህር ላይ ወንብድና ተግባር ነው ሲሉ የኢራን ጦር ኃይሎች የካታም አል-አንቢያ ማዕከላዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ዞልፋጋሪ ተናግረዋል።
▪የጦር መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ መታየት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደመጣስ ይቆጠራል ሲል የኢስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይል ገልጿል።
▪የባህር ወሽመጡ በልዩ ደንቦች መሠረት ለሲቪል መርከቦች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦች ግን አሁንም የተከለከሉ ናቸው ሲሉ ዘቡ አስታውቋል።
▪የኢራን ወደቦች አደጋ ላይ ከወደቁ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ወደብ ደህንነቱ የተጠበቀ አይሆንም ሲል ካታም አል-አንቢያ አስጠንቅቋል።
የዓለም አቀፍ ምላሽ
እንግሊዝ የአሜሪካን የባህር ኃይል እገዳ እንደማትደግፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ገልጸዋል።
ድርጊቱ "ምንም ትርጉም የማይሰጥ" ነው ሲሉ የስፔን መከላከያ ሚኒስትር ማርጋሪታ ሮብልስ ተናግረዋል።
እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመሆን በሆርሙዝ ወሽመጥ የባህር ላይ ትራፊክ እንዲመለስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የባህር ወሽመጡን በኃይል ለመክፈት በሚደረግ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ፈረንሳይ እንደማትሳተፍ የሀገሪቱ የአውሮፓ ጉዳዮች ሚኒስትር ቤንጃሚን ሃዳድ ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ መንግሥት በእገዳው ላይ የመሳተፍ ዕቅድ እንደሌለው የውጭ ጉዳይ እና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ማት ቲስትልትዋይት ገልጸዋል።
የጃፓን መንግሥት ጦሯ በእገዳው ላይ ይሳተፍ ወይም አይሳተፍ እስካሁን ውሳኔ ላይ አለመድረሱን የካቢኔ ዋና ፀሐፊ ሚኖሩ ኪሃራ ተናግረዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X