ታልቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ሉዓላዊነት ተምሳሌት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
18:01 18.03.2026 (የተሻሻለ: 18:34 18.03.2026)
ሰብስክራይብ
ታልቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ሉዓላዊነት ተምሳሌት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል - የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
ግድቡ ፖለቲካዊ ውጥረቶችና ግጭቶች ሲከሰቱ የሚፈጠር የኃይል የዋጋ መናር እና የአቅርቦት እጥረት ተጋላጭነትን የሚቀንስ መሆኑን የድርጅቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ወቅታዊውን የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት የፈጠረውን የኃይል እጥረትን አስመልክተው ለስፑትኒክ አፍሪካ ተናግረዋል፡፡ የነዳጅ ጥገኝነትን እና የውጭ ምንዛሪ ጫናን ከመቀነስ አንጻርም ተመልክተውታል፡፡
“ምዕራባውያን ለምሳሌ የገበያ ጥገኝነት እንዲፈጠር ይሰራሉ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከምዕራብ እና ከምዕራብ ጋራ አጋር ከሆኑ ሀገራት ኢነርጂ እንድትገዛ የሚያስገድዱበት አሠራር አለ።” በማለት የሕዳሴ ግድብ ይህን በነዳጅ ላይ ጥገኛ የመሆን ሁኔታን የሚቀይር የለውጥ ነጥብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ያሉ ከምዕራባውያን ጋር የወገኑ ተቋማት አፍሪካ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እንድትገነባ ፈቃደኞች አይደሉም ሲሉ ዳይሬክተሩ ሞግተዋል።
"... እነዚህ ተቋማት የራሳቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠው ነው የተፈጥሮ ሀብትህን ጭምር እንድታለማ የሚያደርጉት" ሲሉ የተፅዕኖውን ክብደት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ አቅም ህዝቦቿንና አቅሟን አስተባብራ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን መገንባቷ ለኃይል ሉዓላዊነት በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡
"የራሴን እጣ ፈንታ በራሴ መወሰን እችላለሁ የሚል ትልቅ የሥነ-ልቦናም የኢኮኖሚ ነጻነትም ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ስለሆነ የአፍሪካዊ ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ ተብሎ ሲቀነቀን የነበረውን መርህ በተግባር የሚያሳይ ነው።" ብለዋል፡፡
ሞገስ መኮንን በውጭ ኃይል ላይ ጥገኛ የሆኑ ሀገራት ጂኦፖለቲካዊ ቀውሶችና ውጥረቶች በተከሰቱ ቁጥር የውጭ ኃይል መጠቀሚያ መሆናቸው አይቀሬ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ደምድመዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X