ደቡብ አፍሪካ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ቀውስ መባባስ ዙሪያ ከፍተኛ ስጋቷን ገለፀች
17:34 07.03.2026 (የተሻሻለ: 17:44 07.03.2026)

© telegram sputnik_ethiopia
/ ሰብስክራይብ
ደቡብ አፍሪካ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ቀውስ መባባስ ዙሪያ ከፍተኛ ስጋቷን ገለፀች
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "እነዚህ ክስተቶች ግጭቱን በማስፋፋት በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰላምና ደህንነት ላይ ከባድ መዘዝ ያስከትላሉ" ብሏል።
ሚኒስቴሩ አክሎም እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የፈጸሙትን ሕገ-ወጥ ጥቃት በመኮነን፤ ጥቃቶቹ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 2(4)ን የጣሱ እና በሕግ ላይ የተመሠረተውን ዓለም አቀፍ ስርዓት የሚያናጉ መሆናቸውን ጠቁሟል።
በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በተለያዩ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ላይ የወሰደችውን አጸፋዊ እርምጃ ትኮንናለች" ብሏል።
"ኢራን ወታደራዊ ጥቃት ከፈጸሙባት ሀገራት ራሷን የመከላከል መብት ቢኖራትም፤ በባሕረ ሰላጤው የትብብር ምክር ቤት ሀገራት ላይ የወሰደችው እርምጃ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀጽ 51 ስር ከተፈቀደው ጋር የማይጣጣም እና የሀገራቱን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው። በባሕረ ሰላጤው ሀገራት ላይ የተፈጸሙት እነዚህ ጥቃቶች ሰፊ ቀጣናዊ ጦርነት የመቀስቀስ አደጋን ከፍ ያደርጋሉ" ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል።
አክሎም እየተባባሱ የመጡ ድርጊቶች የኢራን የኒውክሌር መርኃ-ግብር ንግግሮችን ጨምሮ የቅርብ ጊዜ ጥረቶችን አደጋ ላይ እንደሚጥሉ አጽንኦት ሰጥቷል። ለቀውሱ ወታደራዊ መፍትሄ እንደሌለ በድጋሚ በማረጋገጥ፤ ውጥረቱ እንዲረግብ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወደሚመራ ድርድር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ፤ "ለሰላማዊ ሰዎች ሞት፣ ለመሠረተ ልማት ውድመት እና ለማኅበረሰቦች መፈናቀል" ምክንያት የሆነው የእስራኤል የሊባኖስ ወታደራዊ ዘመቻ እንዳሳሰባት ገልጻለች።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "እነዚህ ጥቃቶች የሊባኖስን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በእጅጉ የሚጥሱ እና ቀጣናውን የበለጠ የሚያናጉ ናቸው" ብሏል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X