በእስራኤል እና በአሜሪካ በኢራን ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች፡- የቅርብ ጊዜ መረጃዎች

በእስራኤል እና በአሜሪካ በኢራን ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች፡- የቅርብ ጊዜ መረጃዎች
በኩዌት በደረሰ የኢራን የድሮን ጥቃት ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ፣ አምስት ደግሞ "በጽኑ መቁሰላቸውን" የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።
የሄዝቦላህ ታጣቂ ቡድን የኢራኑን ሉዓላዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒን ግድያ "ለመበቀል" በሚል በእስራኤል የጦር ሰፈር ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
ሄዝቦላህ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን ተከትሎ፣ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከ50 በላይ ከሚሆኑ የሊባኖስ መንደሮች ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ አዟል።
በቆጵሮስ የሚገኘው የብሪታንያ ራፍ አክሮቲሪ የጦር ሰፈር "በኢራን ድሮን ሳይሆን አይቀርም" በተባለ ጥቃት መመታቱን የብሪታንያ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።
በባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የሚገኘውን የአሜሪካ ቪክቶሪ ቤዝ የጦር ሰፈርን፣ ሁለት ድሮኖች ኢላማ አድርገውታል ሲሉ የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ኢራን በሀገሪቱ ማዕከላዊ ክፍል ዘመናዊውን የአሜሪካ ኤምኪው-9 ድሮን መትታ መጣሏን ተስኒም የዜና ወኪል ዘግቧል።
ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ውስጥ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን እና በካራጅ ከተማ ተከታታይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን የሃገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ በመጀመሪያው የንግድ ልውውጥ፣ የአሜሪካ ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 75 ዶላር ከፍ ሲል፣ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ ወደ 82 ዶላር አሻቅቧል።
መግለጫዎች
በኢራን ውስጥ በሚደረጉ ወታደራዊ እርምጃዎች "ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደሮች ሊሞቱ ይችላሉ" ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ የገለጹ ሲሆን፣ ዘመቻው ለአራት ሳምንታት ወይም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ሊቆይ እንደሚችልም አምነዋል።
ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር አታደርግም ሲሉ የኢራኑ የደህንነት ኃላፊ አሊ ላሪጃኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
አዲስ የኢራን ሉዓላዊ መሪ "በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ" ሊመረጥ እንደሚችል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ፣ አያቶላህ አሊ ካሜኒ ግድያ እስራኤል እና አሜሪካ ተጠያቂ እንዲሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና የፀጥታው ምክር ቤት እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።
ግጭቱን በውይይት ለመፍታት፣ "የዲፕሎማሲው በር አሁንም ክፍት ነው" ሲሉ የኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አል-ቡሳይዲ አሳስበዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X