የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በሩባያ ማዕድን ማውጫ ለደረሰው አሰቃቂ የመደርመስ አደጋ ሩዋንዳ እና ኤም23ን ተጠያቂ አደረገ
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በሩባያ ማዕድን ማውጫ ለደረሰው አሰቃቂ የመደርመስ አደጋ ሩዋንዳ እና ኤም23ን ተጠያቂ አደረገ
በሰሜን ኪቩ፣ ሩባያ በሚገኘው የማዕድን ቦታ ጥር 11 ቀን በተከሰተው ናዳ ቢያንስ ከ200 እስከ 226 የሚደርሱ ሰዎች፤ አብዛኞቹ ባሕላዊ የማዕድን ቆፋሪዎች፣ ሴቶች እና ህጻናት፤ መሞታቸውን እና ብዙዎች በአደገኛ ጉድጓዶች ውስጥ በህይወት እያሉ መቀበራቸውን የሀገሪቱ መንግሥት እና የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቁልፍ ነጥቦች፦
◻ የማዕድን ቦታው ከየካቲት 2025 ጀምሮ ማንኛውም የማውጣት ሥራ እንዳይከናወንበት "ቀይ" ተብሎ የተፈረጀ ቢሆንም በሩዋንዳ እና በኤም23/ኤኤፍሲ በዝባዥነት በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ሆኖ ሕገ-ወጥ ቁፋሮው ሲካሄድ ቆይቷል ሲል የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ገልጿል።
◻ ኪንሻሳ በየወሩ ከ112 እስከ 125 ቶን የሚደርስ "ኮልታን" ከሩባያ እየወጣ "የጦርነት ኢኮኖሚ" ብላ ወደገለጸቻት ሩዋንዳ በቀጥታ ይላካል ብላለች።
◻ ሰኔ 2025 በተመሳሳይ ከ300 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፤ ንጹሐንን ለአደጋ የማጋለጥ ተደጋጋሚ ድርጊት ማስረጃ እንደሆነ ጠቁሟል።
◻ ሩዋንዳ በ2025 የመጀመሪያ አጋማሽ የኮልታን ወጪ ንግዷን "ከ200 በመቶ በላይ" ማሳደጓ፤ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ካሉ አካባቢዎች የሚወጡ የኮንጎ ማዕድናትን "በሕገ-ወጥ መንገድ እየተዘዋወሩ" እንደሆነ ማስረጃ ነው ስትል ኮንጎ ገልጻለች። ሩዋንዳ እስካሁን ለቀረበባት ክስ ምላሽ አልሰጠችም።
◻ የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ ፓትሪክ ሙያያ፤ በሩባያ የሚገኙ የማዕድን ቦታዎች ከሚያዝያ 2024 እስከ መጋቢት 2025 እንዴት እንደተስፋፉ የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ በማድረግ፤ የኪንሻሳን የ "መዋቅራዊ ዘረፋ" ክስ አብራርተዋል። ( ቪዲዮ 2)
◻ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የማዕድናት ዱካ መከታተያ ዘዴዎች "በግልጽ መክሸፋቸውን" አውግዛለች፤ የማዕድን ቦታው የ "ቀይ" ማስጠነቀቂ ውስጥ መስፈሩን ችላ ብለው የሚገዙ የውጭ ሀገር ገዢዎችንም ኮንናለች።
◻ የነፍስ አድን ሥራው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።
◻ በኤም23 ቁጥጥር ስር ያሉ ባለሥልጣናትን የጠቀሱ ዘገባዎች፤ የተረፉት ሰዎች በጎማ ከተማ ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
◻ አንዳንድ ማዕድን አውጪዎች በሌሎች ጉድጓዶች ውስጥ ወደ ሥራ እንደተመለሱ እና ሱቆችም እንደገና መከፈታቸውን የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ያነጋገሯቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ℹ ለኤሌክትሮኒክስ እና ለጠፈር ምርምር ኢንዱስትሪዎች ወሳኝ ግብዓት ከሆነው የኮልታን ምርት፤ 15 በመቶውን ለዓለም የምታቀርበው ሩባያ፤ ከ2024 ጀምሮ በኤም23/ኤኤፍሲ አማፂያን ቁጥጥር ስር ትገኛለች።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X