ቡና ከኢትዮጵያ ቢጠፋ ከዓለምም ይጠፋል - የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር
10:22 19.01.2026 (የተሻሻለ: 11:04 19.01.2026)

© telegram sputnik_ethiopia
/ ሰብስክራይብ
ቡና ከኢትዮጵያ ቢጠፋ ከዓለምም ይጠፋል - የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር
ኢትዮጵያ በዱባይ በተከፈተው ዓለም አቀፍ የቡና አውደ ርዕይ 26 የቡና አምራችና ላኪ ድርጅቶችን ይዛ እየተሳተፈች ነው።
በዚህ ሁነት ዙሪያ ለስፑትኒክ አፍሪካ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ፤ አውደ ርዕዩ የሀገሪቱን ቡና ለማስተዋወቅ በጣም ጠቃሚ ነው ብለዋል።
በጣዕም መለያ ብዛት ተወዳዳሪ የሌላት ሀገሪቱ፤ ምልክቷ (ብራንድ) ላይ አበክራ ብትሠራ ልዩ የቡና ሀገርነቷን ይበልጥ እንደምታረጋግጥ ገልጸዋል።
"የእኛን ለየት የሚያደርገው ከ10 ሺህ በላይ የቡና ዓይነት ስላለ፤ ቀምሰኸው የማታውቀው የቡና ዓይነት ልታገኝ ትችላለህ። በጣዕም መለያ መንገዶች ስትሄድ የኢትዮጵያን ቡና ያህል ብዙ የጣዕም መለያ ያለው ልታገኝ አትችልም።"
የቡና ዘርፍ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት ያስመዘገበውን የወጪ ንግድ ገቢ ያነሱት አቶ ግዛት ወርቁ፤ ይህንን አካሄድ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
በአውድ ርዕዩ ለጨረታ የሚቀርቡ የኢትዮጵያ የቡና ዓይነቶች የማሸነፍ ዕድላቸውን በተመለከተ ሲናገሩ
"ሁሌም የኢትዮጵያ ቡና የማሸነፍ ዕድል አለው። ምርጥ ቡናዎች አሉን። በጥንቃቄ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ቡናውን በደንብ ሠርቶ በደንብ ይዞት ከሆነ የማሸነፍ ዕድላችን መቶ በመቶ የሚያጠራጥር አይደለም። በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ቢጠፋ ከዓለም እንደሚጠፋ ታውቃለህ? ምክንያቱም ምንጩ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እና የኢትዮጵያ ቡና ያሸንፋል" ብለዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X