ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል - ግብፃዊ የሕግ ባለሙያ

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል - ግብፃዊ የሕግ ባለሙያ
2025 ከተዓማኒነት አኳያ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ታሪክ እጅግ አስከፊ ከሆኑ ዓመታት አንዱ እንደነበር የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያው መሐመድ መህራን ለስፑትኒክ ገልጸዋል።
በፖለቲካ ጫና፣ በጉዳዮች አያያዝ ላይ የሚታይ አድልዎ፣ የውሳኔ ማስፈጸሚያ ዘዴዎች አለመኖር እና አባል ሀገራት የፍርድ ቤቱን ውሳኔዎች ባለማክበራቸው በርካታ ውሳኔዎቹ ትርጉም አልባ ሆነዋል ሲሉ ባለሙያው አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እውነተኛ የማስፈጸም ሥልጣን ስሌለው፤ በሀገራት ፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ ትብብር ጥገኛ እንደሆነ መህራን ጠቁመዋል። ይህም አንዳንድ ሀገራት ምንም ዓይነት ቅጣት ሳይደርስባቸው የፍርድ ቤቱን ውሳኔዎች ችላ እንዲሉ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
ለዚህም ፍርድ ቤቱ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ ያወጣውን የእስር ትዕዛዝ ማስፈፀም አለመቻሉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዮችን ከፖለቲካ ጋር ማያያዙ፣ በቅርቡ አሜሪካ በፍርድ ቤቱ ላይ የጣለችው ማዕቀብ እና አንዳንድ ሀገራት አባልነታቸውን ማቋረጣቸው የተቋሙ ተዓማኒነት ይበልጥ እንዲዳከም እና ተቋማዊ አፈጻጸሙ እንዲቀንስ ማድረጉን በመግለፅ ሀሳባቸውን ደምድመዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X