የወቅቱ የሱዳን ግጭት የታሪካዊው ትግል ቀጣይ ምዕራፍ እና አዲስ የነፃነት ተጋድሎ ነው - አል-ቡርሃን
የወቅቱ የሱዳን ግጭት የታሪካዊው ትግል ቀጣይ ምዕራፍ እና አዲስ የነፃነት ተጋድሎ ነው - አል-ቡርሃን
ሱዳን የአፍሪካ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ መሪ በመሆን የተጫወተችውን ታሪካዊ ሚና በማስታወስ፤ 70ኛ የነፃነት በዓሏን እያከበረች ትገኛለች።
ካርቱም ከቅኝ አገዛዝ በኋላ ሉዓላዊነታቸውን የተቀዳጁ የመጀመሪያዎቹ የአኅጉሪቱ ሀገራትን የተቀላቀለችው እ.አ.አ ጥር 1፣ 1956 ነበር።
እ.ኤ.አ 1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች አባል የነበረችው ሱዳን፤ በመላው አኅጉሪቱ ለሚገኙ የነፃነት ንቅናቄዎች ንቁ ድጋፍ አድርጋለች፡፡ ለአብነትም ለአልጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የነፃነት ትግል ዲፕሎማሲያዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ሰጥታለች።
የነጻነት በዓሉ፤ ሀገሪቱ በብሔራዊ ጦር ሠራዊቱ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይል አማፂያን መካከል እ.አ.አ በሚያዝያ 15፣ 2023 በጀመረው እና አሁንም በቀጠለው አስከፊ ውስጣዊ ግጭት እየታመሠች ባለችበት ወቅት የመጣ ነው።
የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን በካርቱም ከሚገኘው ሪፐብሊካን ቤተ-መንግሥት ሆነው ባደረጉት ንግግር፤ ለሱዳን ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ወታደሮቻቸውን አወድሰዋል።
ከአል-ቡርሃን ንግግር የተወሰዱ ዋና ዋና ነጥቦች፦
◻ ስለሚካሄደው ጦርነት፦ "በመላው ሱዳን ለሚገኘው ሕዝባችን ድል መቃረቡን እናረጋግጣለን... ይህ የክብር ጦርነት አንድ አድርጎናል።"
◻ ስለ ታሪክ ቀጣይነት፦ "አባቶቻችን ቅኝ ገዥውን ለማባረር እ.ኤ.አ በ1885 እና 1956 እንደተሰባሰቡት ሁሉ እኛም አማፂያኑን፣ ከዳተኞችን እና አነሳሾችን ከምድራችን ለማስወጣት ዳግመኛ እንሰባሰባለን።"
◻ ለፖለቲካ ኃይሎች የተላለፈ መልዕክት፦ "በሩ አሁንም ክፍት ነው... የብሔራዊ እርቅ በሮች በሰፊው እንደተከፈቱ ናቸው። ይህች ሰፊ ሀገር ለሁሉም ሰው የሚሆን ቦታ አላት።"
አል-ቡርሃን በበዓሉ መልዕክታቸው ሱዳን በመላው አፍሪካ ለነፃነት ንቅናቄዎች ስታደርገው የነበረውን ድጋፍ በመዘከር፤ የወቅቱን ትግል "ከአረመኔነት፣ ከጭካኔ እና በአዲስ መልክ ከመጣ ቅኝ አገዛዝ" ለመላቀቅ የሚደረግ አዲስ የነፃነት ተጋድሎ ሲሉ ገልጸውታል።
የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ባጋራው ቪዲዮ የሀገሪቱ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ኢስማኢል አል-አዝሃሪ የነፃነት ሰንደቅ ዓላማን የሰቀሉበትን ታሪካዊ ትዕይንት ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ የሱዳን የታሪክ ምዕራፎች ቀርበዋል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X
