አፍሪካ በ2026 ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዴት ማረጋገጥ ትችላለች?
አፍሪካ በ2026 ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንዴት ማረጋገጥ ትችላለች?
ናይጄሪያዊው የዘርፉ ባለሙያ ለዚህ ጥያቄ ተጨባጭ ምላሽ ይሆናሉ ያሏቸውን ተግባራዊ እርምጃዎች ጠቁመዋል፡፡
የኢኮኖሚ ስኬት የሚገኘው በአጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ መረጋጋት እና መደበኛው ዜጋ ተጠቃሚ በሚሆንባቸው ኢንቨስትመንቶች መካከል ሚዛን በመጠበቅ ነው ያሉት ናይጄሪያዊው ደራሲ እና የፋይናንስ አማካሪ ሻጎን ኦባሱን (ዶ/ር)፤ የናይጄሪያን የቅርብ ጊዜ የለውጥ ተሞክሮዎች በመጥቀስ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ኦባሱን (ዶ/ር) ከስፑትኒክ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ የአኅጉሪቱ መንግሥታት ትኩረት ሊሰጡባቸው የሚገቡ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፦
◻ ከማኅበራዊ ጥበቃ ጋር ቅደም ተከተልን የጠበቁ ማሻሻያዎች፦ እንደ ድጎማ ማንሳት ወይም የገንዘብ ምንዛሬ ማስተካከያ ያሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በጥንቃቄ በደረጃ መከናወን አለባቸው። በተጨማሪም ዜጎች ለከፋ ድህነት እንዳይጋለጡና በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት እንዳይሸረሸር ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ቀጥተኛ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።
◻ የግል ዘርፉን የሚያነቃቁ የመንግሥት ኢንቨስትመንቶች፦ መንግሥታት የግል ባለሀብቶችን የሚያበረታቱ፤ እንደ የገጠር መንገዶች፣ አስተማማኝ የኢንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቀዝቃዛ ምርት ማከማቻዎች እና የባቡር መስመር መሠረተ ልማቶች ላይ ወጪያቸው እንዲያተኩር ማድረግ ይኖርባቸዋል።
◻ የተቋማት ግልፅነት፦ ስለ ሀገራዊ ዕዳ፣ ገቢ እና የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች መደበኛ መረጃዎችን ይፋ ማድረግ በገበያው እና በዜጎች ዘንድ ተዓማኒነትን ይፈጥራል።
◻ ከመረጋጋት ወደ ኢንዱስትሪ ፖሊሲ፦ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ መረጋጋት ከተረጋገጠ በኋላ ሀገራት ዘላቂና ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንደ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ፣ ቀላል ማኑፋክቸሪንግ እና የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው።
በተጨማሪም፤ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅ እንዲጠበቅ የኢኮኖሚ አማራጮችን በተለይም የዲጂታል አገልግሎቶችና ቀጣናዊ አምራች ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ኦባሱን አሳስበዋል።
"ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መርሁ ቀላል ነው" ሲሉ ደምድመዋል። "ተዓማኒነት ያለውን ማክሮ ፖሊሲ ለድሆች ከሚጠቅም ግልጽ ኢንቨስትመንት ጋር ማጣመር። ይህ ቅንጅት የመቋቋም አቅምን ያጠናክራል፤ የለውጥ ጉዞውንም ዘላቂ ያደርገዋል።"
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X