የሩሲያ እና አፍሪካ አጋርነት የልማት እንጂ የሀብት ብዝበዛ አይደለም - ላቭሮቭ

የሩሲያ እና አፍሪካ አጋርነት የልማት እንጂ የሀብት ብዝበዛ አይደለም - ላቭሮቭ
"ሩሲያ የራሷ ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሏት በመሆኑ አፍሪካን እንደ የጥሬ ዕቃዎች ማውጫ አድርጋ አትመለከትም" ሲሉ የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሩሲያ-አፍሪካ ትብብር መድረክ ሁለተኛ የሚኒስትሮች ጉባኤን አስመልክቶ ባሳተሙት ጽሑፍ ላይ አስፍረዋል፡፡
በተቃራኒው ሞስኮ የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ሀብት እንዲያዳብሩ፣ የኢንዱስትሪ አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ እና የኑሮ ጥራትን እንዲያሻሽሉ ለሚያግዙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡
የኢኮኖሚ ትስስር በፍጥነት እየሰፋ ነው። ከአፍሪካ ጋር የንግድ ልውውጥ ያለማቋረጥ እያደገ መጥቶ ከ2019 ጀምሮ ከአንድ ተኩል በላይ በመጨመር ባለፈው ዓመት ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
ላቭሮቭ “በዚህ አይገደብም" ሲሉ አፅንዖት በመስጠት፤ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ጋር እያደገ የመጣውን ንግድ፣ የአፍሪካ ምርቶች በሩሲያ ገበያ ሰፋ ያለ ተደራሽነት እያገኙ እና በብሔራዊ ገንዝቦች ንግድ እየተፈፀመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሩሲያ በ19 የበይነ መንግሥት ኮሚሽኖች የረጅም ጊዜ ትብብርን ትደግፋለች እንዲሁም በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አዳዲስ እድሎች እንዳሉ ትመለከታለች፡፡ ለሚቀጥሉት አስርት ዓመታት የተነደፉት እነዚህ ተነሳሽነቶች፤ በአፍሪካ በሶቪየት ድጋፍ የተገነቡ ከ300 በላይ የኢንዱስትሪ እና የመሠረተ ልማት ተቋማትን ጨምሮ በታሪካዊ ትብብር ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡
የሰብዓዊ እና የቴክኖሎጂ ትብብሮች ማዕከላዊ ሆነው ይቀጥላሉ፡፡ ሩሲያ በግብርና፣ በጤና አጠባበቅ እና በየአደጋ ጊዜ መከላከል እና ምላሽ አሰጣጥ ላይ የምታደርገውን ድጋፍ ቀጥላለች፡፡ የሩሲያ የሞባይል ላቦራቶሪዎች በመላ አኅጉሪቱ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡
በሌላኛው ምሰሶ፤ የትምህርት ዘርፍ፤ ሩሲያ ለአፍሪካ የምታቀርበው የነፃ ትምህርት ዕድል ኮታ ወደ ሶስት እጥፍ ገደማ በማደግ ከ5,300 በላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ32,000 በላይ የአፍሪካ ተማሪዎች በሩሲያ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡
ላቭሮቭ ሩሲያ በሁለትዮሽ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ የባለብዙ ወገን ተቋማት፤ በተለይም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ለመተባበር ዝግጁ እንደሆነች እና በጋራ እድገት፣ ሉዓላዊነት እና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ አጋርነትን እንደምታጠናክር አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X