በቀዶ ህክምና 19 ኪሎግራም የማህጸን እጢ ከአንዲት እናት ሆድ ውስጥ ማውጣቱን የወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ
12:01 15.12.2025 (የተሻሻለ: 12:04 15.12.2025)

© telegram sputnik_ethiopia
/ ሰብስክራይብ
በቀዶ ህክምና 19 ኪሎግራም የማህጸን እጢ ከአንዲት እናት ሆድ ውስጥ ማውጣቱን የወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ
በገጠራማ አካባቢ የምትኖር የ28 ዓመት ወጣት ወሊድ ከፈፀመች 30 ቀናት በኋላም የሆዷ ግፊት ሊቀንስ ባለመቻሉ በወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል በተደረገ ቀዶ ጥገና እጢው መገኘቱ ተገልጿል፡፡
ከወሊድ በኋላ የሚሠሩ ቀዶ ጥገናዎች የእርግዝና ጊዜው ካለፈ ከስድስት ሳምታት በኋላ መሠራት እንዳለበት ቢመከረም እናትየዋ ላይ በነበረው ህመም ሳቢያ በወለደች በአንድ ወሯ ኦፕሬሽን እንደተሠራላት ህክምናውን የሰጡት ዶክተር ጁሃር መሐመድ ተናግረዋል፡፡
"በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ከእምብርቷ በላይ አልፈን ነው የሠራነው። በጣም ትልቅ እጢ ሲሆን ይጠማዘዛል ተብሎ ባይታሰብም ግን ሁለት ጊዜ ተጠማዞ ነው ያገኘነው" ሲሉ ታህሳስ 1 ቀን 2018 በተሠራው ቀዶ ጥገና ያጋጠማቸውን አስረድተዋል፡፡
🩺 እናትየዋ ሙሉ የእርግዝና ክትትል ባለማድረጓ የተነሳ ሳይታወቅ እጢውን ከጽንስ ጋር ተሸክማው ማደጉን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
“እጢው ከወጣ በኋላ በፌስታል የተቋጠረ ነው የመሰለው። ግን የራሱ የእጢው ከረጢት ነው። በራሱ ከረጢት ነው ቋጥረን ያወጣነው። በጣም ትልቅ ስለሆነ ባንዴ አይወጣም፤ ቀስ እያልን እየገፋን አወጣነው። ስንመዝነው ማመን አልቻልንም፤ ሳፋውን ሞልቶ አልፏል። 19 ኪሎ ግራም ነው። እንደዚህ አይነት ገጠመኝ አጋጥሞን አያውቅም” ብለዋል፡፡
ታካሚዋ ከቀዶ ጥገናው በኃላ በሙሉ ጤንነት ላይ ሆና፤ ልጇንም በማጥባት ላይ እንደሆነች ባለሙያውን ጠቅሶ የሀገር ውስጥ ሚዲያ ዘግቧል፡፡
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X