ዚምባብዌ የመጀመሪያውን ተንሳፋፊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በሚቀጥለው ዓመት መገንባት ልትጀምር ነው
15:45 10.12.2025 (የተሻሻለ: 15:54 10.12.2025)
© telegram sputnik_ethiopia
/ ሰብስክራይብ
ዚምባብዌ የመጀመሪያውን ተንሳፋፊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በሚቀጥለው ዓመት መገንባት ልትጀምር ነው
"የካሪባ ተንሳፋፊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ለዚምባብዌ አዲስ ልማት ነው። የመጀመሪያው ተንሳፋፊ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ሲሆን፣ ሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች የውሃ ላይ የፀሐይ ኃይል ከየብስ የበለጠ ውጤታማ እንደሆነ ነግረውናል" ሲሉ የመሬት ሚኒስትሩ አንክስየስ ማሱካ ማክሰኞ ዕለት ከካቢኔ ስብሰባ በኋላ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
600 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ይህ ፕሮጀክት በዓለማችን ትልቁ ሰው ሠራሽ ሐይቅ፤ ካሪባ ላይ በሦስት ምዕራፎች ይገነባል፡፡ ዚምባብዌ ሐይቁን ከጎረቤት ዛምቢያ ጋር የምትጋራ በመሆኑ ፕሮጀክቱ እንዲቀጥል ከሁለቱም ሀገራት ይሁንታ ያስፈልጋል ተብሏል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ 150 ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ እና በ2026 ሁለተኛ ሩብ ዓመት እንደሚጀመር ይጠበቃል።
5 ዓመታት የግንባታ ሂደት የተያዘለት ፕሮጀክቱ፤ ጠቅላላ ወጪው 650 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት ማሱካ ገልጸዋል።
ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ የሚያጋጥማት ዚምባብዌ፤ ባለፈው ዓመት ባጋጠመው ድርቅ ከግማሽ በላይ የሀገሪቱን ኃይል አቅርቦት በሚሸፍነው የካሪባ ግድብ የውሃ ኃይል ቀንሶ ችግሩ ይበልጥ ተባብሶ ነበር። ካሪባ በአሁኑ ወቅት 550 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ሲሆን ይህም ማመንጨት ከሚችለው 1,050 ሜጋ ዋት አቅም በእጅጉ ያነሰ ነው።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X