ታንዛኒያ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማን የድህረ-ምርጫ የመብቶች ጥሰት በሚል ወደ ክርክር ማምራቱን በውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘች

ታንዛኒያ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማን የድህረ-ምርጫ የመብቶች ጥሰት በሚል ወደ ክርክር ማምራቱን በውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘች
አገሪቱ የአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ከታንዛኒያ ጋር ሳይመክር በድህረ ምርጫ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል ለመወያየት ያዘጋጀውን ዕቅድ ተከትሎ እየጨመረ የመጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በፅኑ አውግዛለች።
በብራሰልስ የሚገኘው የታንዛኒያ ኤምባሲ ህዳር 16 በፃፈው የዲፕሎማቲክ ደብዳቤ፤ በስብሰባው ላይ በተለይም ከምርጫ በኋላ ስለተፈጸሙ ግድያዎች እና በተቃዋሚው መሪ ቱንዱ ሊሱ ጉዳይ ላይ በተደረጉ ውይይቶች ላይ "ስጋቱን" ገልጿል።
የታንዛኒያ መንግስት ይህ ውሳኔ የሳሞአ የውይይት፣ የምክክር እና የጋራ መከባበር ስምምነት መርሆዎችን እንደማይከተል አስታውቋል። ለአንድ ወገን ያደላ እርምጃ የአስርተ ዓመታት ትብብርን አደጋ ላይ ይጥላል ሲልም አስጠንቅቋል።
ባለስልጣናት እና ተንታኞች ይህ እርምጃ የውጭ አካላት በሰብአዊ መብት ስም የአገር ውስጥ ፖለቲካን ለመቅረፅ ከሚሞክሩበት ሰፊ ስርዓት አንዱ አካል ነው ማለታቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገባ አመላክቷል።
“አንድ አካሄድ እየተፈጠረ ነው፤ ሉዓላዊ አገራት ከኃያላን አገራት ፍላጎት ጋር የማይጣጣሙ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ውሳኔዎችን ሲያደርጉ፣ ግፊት ማድረጊያ መሳሪያዎች ይወጣሉ” ሲሉ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ማስጠንቀቃቸው ተዘግቧል።
ተቺዎች በታንዛኒያ ላይ ስላለው ከፍተኛ ትኩረት እና በሱዳንና ጋዛ ላይ ስላለው አንጻራዊ ዝምታ በማጣቀስ የመርጦ አልቃሽ አድሎአዊነትን አጉልተው በማንሳት ጥያቄዎችን ያነሳሉ።
“ይህ ስለ ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎቶች እንጂ ስለ ሰብአዊ መርሆዎች አይደለም” ሲሉ አንድ የቀጣናው ተንታኝ መናገራቸው ተዘግቧል።
ታንዛኒያ ነፃ የምርመራ ኮሚሽን ማቋቋሟን በመግለፅ የውጭ ጫና የአገር ውስጥ ሂደቶች ከመጠናቀቃቸው በፊት ሊያስተጓጉል እንደሚችልም አስጠንቅቃለች። አገሪቱ የአውሮፓ ሕብረት ስብሰባውን እንዲያራዝም አልያም ድምጿን የማሰማት ዕድል እንዲሰጣት ጠይቃለች፤ ሆኖም እስካሁን በግልጽ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ይህ ውዝግብ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች የእጀ ዙር ቅኝ ግዛት የፖለቲካ ተጽዕኖ ብለው ከሚገልጹት እና በአህጉሪቱ እየተስፋፋ ካለው ተቃውሞ ጋር የተያያዘ ነው ሲል የዜና አውታሩ ዘግቧል።
የዚህ ያለመግባባት ውጤት ታንዛኒያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን የወደፊት ግንኙነት በመበየን ወደፊት ግንኙነቱ በውይይት ወይም በአንድ ወገን ውሳኔ የሚገለጽ ነው የሚለውን የሚፈትን ይሆናል ሲል መገናኛ ብዙሃኑ ዘግቧል።
ስፑትኒክ ኢትዮጵያ | መተግበሪያ | X