ዶ/ር ወንደወሰን አሰፋና መስከረም አበራን ጨምሮ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 24 ተከሻሾች የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ

ሰብስክራይብ
ፍርድ ቤቱ የተከሻሾቹን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ተከሳሶቹ የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ/ለ/፣ 35 እና 38 እና የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/ 2012 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ የህግ ክልከላ አለበት በሚል መሆኑን ፋና ዘግቧል።
ዐቃቤ ህግ በምክንያትነት ያቀረበውን ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በሚሰጠው ውጤት ተካፋይ በመሆን፣ የሽብር ድርጊት በቀጥታ በመምራት፣ በማደራጀት የተግባር ተሳትፎ መሰረት 217 ሰዎች ህይወት ያለፈበት እና የተከሰሱበት አንቀጽ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ድንጋጌ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ጥያቄያቸው በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 63 መሰረት ውድቅ ይደረግ በማለት ተከራክሯል።
የተከሳሽ ጠበቆች ደግሞ ተከሳሾቹ በቀረበባቸው የወንጀል ክስ በጋራ እንጅ እያንዳንዳቸው ሰው ገድለዋል ተብሎ የቀረበ ዝርዝር የለም በማለት የዋስትና መብታቸው ሊከለከል አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።
በዚህ መነሻ የግራ ቀኙን ክርክር የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የዋስትና መብት ከተከሰሱበት ድንጋጌ አንጻር የህግ ክልከላ ያለበት መሆኑን ጠቅሶ ውድቅ አድርጓታል። ተከሳሾቹ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አራት ጋዜጠኞች በመገኛና ብዙሃን አዋጅ መሰረት የዋስትና መብታችን ሊታይ ይገባል ብለው የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ በሙያ ተሳትፎ ሳይሆን በሽብር ድርጊጊት ተሳትፎ ነው በማለት ውድቅ አድርጎታል ብሏላ ዘገባው፡፡
ከተከሳሾች መካከል ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣መስከረም አበራ፣ መሰረት ቀለመወርቅ (ዶ/ር፣ ሲሳይ አውግቸው (ረ/ፕ)፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ መንበረ አለሙ፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ ማስረሻ እንየው፣ ታደሰ ወንዳይነው፣ አንደበት ተሻገር እና ዳዊት አባቡን ጨምሮ 24 ግለሰቦች በችሎት ተገኝተው በፍርድ ቤቱ የተሰጠውን ብይን ተከታትለዋል።
ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ”መነሻችን አማራ መድረሻችን ኢትዮጵያ” በሚል የፖለቲካ እና የርዕዮት አላማ ለማራመድ በማሰብ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለውን መንግስት በተለያየ ወታደራዊ ስልት እና ስትራቴጅ በመንደፍ፣ የአማራ ክልል የሚዋሰኑባቸውን መንገዶች መዝጋት፣ ህዝብን ማሸበር እና መንግስትን አስገድዶ ከስልጣን ማውረድ የሚሉ የሽብር ተግባር ድርጊቶችን ጠቅሶ በክሱ ላይ ማስፈሩ ይታወሳል።
አዳዲስ ዜናዎች
0