በሰሜናዊ ናይጄሪያ የተስፋፋው ጎርፍ የምግብ ዋስትናን አደጋ ላይ ጥሎ ቀውስ እንዳያስነሳ ስጋት ፈጥሯል ተባለ የጣለው ከባድ ዝናብ በ10 የናይጄሪያ ግዛቶች፤ በዋናነት ደረቃማ በሆነው ሰሜናዊ ክፍል የጎርፍ መጥለቅለቅ አስከትሎ፤ ከባድ የምግብ ዋስትና ስጋት በመፍጠር ቀውስ ሊያስነሳ ይችላል ተብሏል። ጎርፉ የማሳ እህሎችን በማጥለቅለቅ በቅርቡ ከተከሰተው ድርቅ እያገገሙ ያሉ አርሶ አደሮችን መልሶ አደጋ ውስጥ በመክተት ሁኔታዎችን አባብሷል። ባለሙያዎች እያንዣበበ ስላለው የምግብ ስጋት ያስጠነቀቁ ሲሆን መንግሥት የአደጋ ግዜ አስቸኳይ አዋጅ እንዲያውጅ እና ርሃብን ለመከላከል ለአደጋው የሚውል ሀብት እንዲያዘዋወር አሳስበዋል። የጎርፍ አደጋው የተለያዩ ግዛቶችን ማለትም ካኖ፣ ጂጋዋ፣ ዛምፋራ፣ ባውቺ፣ ሶኮቶ፣ ዮቤ እና ናሳራዋን ያጠቃ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሄክታር ሰብሎች ወድመዋል። ጎርፉ በሌሎች የምዕራብ እና የማዕከላዊ አፍሪካ ክፍሎች እየተስተዋለ ሲሆን በጊኒ፣ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኮትዲቯር፣ ላይቤሪያ፣ ማሊ፣ ቶጎ እና ቻድ ሞት፣ የአካል ጉዳት እና መፈናቀል እንዳደረሰ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ የጎርፍ አደጋው በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ምክንያት እንደተከሰተ በመግለጽ ተጨማሪ ህይወት እንዳይጠፋ እና የሰዎችን መከራ ለማቅለል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል። ስፑትኒክ ኢትዮጵያን ይወዳጁ @sputnik_ethiopia